Monday 30 September 2013

ግሸን ደብረከርቤ ዳግማዊት ጎልጎታ

እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል በሰላም አደረሰን !

ግሸን ከደሴ ከተማ 82ኪ.ሜ ርቀት ላይ በወሎ ክ/ሐገር በአንባሰል ወረዳ ውስጥ በሃይቅ እና በመቅደላ በደላንታና በየጁ መካከል በበሽሎ ወንዝ አዋሳኝ ከፍተኛ በሆነ ተራራ ላይ የምትገኝ ገዳም ናት::
የበሸሎን ወንዝ ተሻግረን ሰማይ ጥግ የደረሱ የሚመስሉትን ተራሮች ወጥተን በስተመጨረሻ መግቢያ አንድ በር የሆነ እና ከተራራው አናት ላይ በሚገኝ ስፋራ ላይ በ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም የታነጸ እና ግማደ መስቀሉ የሚገኝበት የ እግዚአብሔር አብ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ::
በ1942 ዓ.ም አቡነ ሚካኤል ጳጳስ ዘጎንደር ከዚህም ጋር ''መንፈሳዊ መናኝ'' በመባል የሚታወቁት ደገኛ አባት ያሰሩት ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንም ይገኛል::

ግሸን ይህን የአሁኑን መጠሪያ ስም ከማግኘትዋ በፊት በተለያየ መጠሪያ ስሞች ትታወቅ ነበር::
በመጀመሪያ በአጼ ድልነአድ ዘመነ መንግስት በ896ዓ.ም ሃይቅ ደብረ እስጢፋኖስ ሲመሰረት ''ሐይቅ ደብረ ነጎድጉዋድ'' ተብሎ ሲሰየም ግሸንም በሃይቅ ግዛት ውስጥ ስለሆነች ስምዋ ''ደበረ-ነጎጉዋድ'' ተባለች::
ይህን መጠሪያ ስምዋን እንደያዘች እስከ አስራአንደኛው ክ/ዘመን ድረስ ቆየች:: በ11ኛው ክ/ዘ ላይ በኢትዮጵያ ነግሶ የነበረው ጻድቁ ንጉስ ላሊበላ ከቁዋጥኝ ድንጋይ ፈልፍሎ የሰራው ቤተ መቅደስ በእግዚአብሔር አብ ስም ይጠራ ስለነበር ግሸንም ''ደብረ እግዚአብሔር'' ተብላ መጠራት ጀመረች:: ነገር ግን በዚህ ስም በመጠራት ብዙም ሳይቆይ ስምዋ ተለውጦ '' ደብረ ነገሥት'' ተባለች:: ደብረ ነገስት የተባለችውም ነገስታቱ ይማጸኑባት የክብርና የማእረግ እቃዎች ያስቀምጡባታል; የነገስታቱ የመሳፍንቱ ልጆችም የቤተ መንግስት አስተዳደር የሚማሩበት ስፍራ ስለነበረች ነው::
እንደገና ደግሞ በ1446ዓ.ም ኢትዪጵያዊው ፈላስፋ እየተባሉ በሚጠሩት በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግስት ግማደ መስቀሉ መጥቶ በዚህ ቅዱስ ስፍራ ሊያርፍ ደብረ- ነግሥት መባልዋ ቀርቶ ''ደብረ- ከርቤ'' ተባለች:: የደብርዋ አስተዳዳሪዋ የማዕረግ ስም ስም ''መምህር እስራኤል ዘደብረ ከርቤ'' ይባል ነበር::
ዓጼ ዘርያቆብ ግማደ መስቀሉን አሸክመው እየገሰገሱ ከብዙ ድካምና ፍለጋ በሁዋላ ወደ ተራራዋ
በመምጣታቸው ''ገሰገሱ'' ከሚለው ቃል በግዕዝ
''ጌሠ'' የሚል ትርጉዋሜ ያለው በመሆኑ ከ''ጌሠ'' በጊዘ ብዛት ግሸን የሚል ቃል በመፍጠሩ ''ግሸን'' የሚለው ስያሜ ሊሰጣት ችሉአል::
ግሸን ማርያም የስም ስያሜዋ ይህን ይምሰል እንጂ የቦታው መገኘት የቆየ ታሪክ አለው::
ዓጼ ዘርዓ-ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ይዘው ከመምጣታቸው ከ932 አመታት በፊት ; ቅዱስ ላሊበላም ደበረ- እግዚአብሔርን ከመመስረቱ ከ583 አመት በፊት ; እነ አባ ኢየሱስ ሞዓ ሃይቅ ደብረ ነጎድጉዋድን ከመመስረታቸው 349 አመት አስቀድሞ በአንድ ደገኛ አባት ተመሰረተች::
ለዓጼ ካሌብ እንደ ነፍስ አባት/የንስሃ አባት ሁነው የሚያገለግሉት አባ ፍቃደ ክርስቶስ የሚባሉት መንፈሳዊ መናኝ በየመን በሃገረ ናግራን ላይ ይኖሩ ስለነበር በናግራን ተራራ ላይ የሚገኙ ሁለት ጽላቶችን ኢትዮጵያን ወስደው እንዲያኖሩ ከፈጣሪያቸው በጸሎት እንደተገለጸላቸው ለንሥሃ ልጃቸው ለዓጼ ካሌብ በመናገራቸው ንጉሱም ፈቅደው አባ ፍቃደ ክርስቶሥም ሁለቱን ጽላቶች አሸክመው ሸሎ ወንዝን ተሻግረው አቀበቱን ወጥተው ወደ መስቀለኛው አምባ ጥግ ሲደርሱ ወደ አምባው ጫፍ ለመውጣት ሰርጥ ሲፈልጉ የአምባውን ዙሪያ በገደሉ ላይ ንብ ሰፍሮ የማሩ ሰፈፍ ጨረቃ መስሎ በማየታቸው የአካባቢውን እና የእግዚአብሔርን ተፈጥሮ ስጦታ ሲያደንቁ ይህስ ''አምባ ''አሰል'' ነው በማለት ተናገሩ:: ''አሰል'' የሚለው ቃል በአረብኛ ''ማር'' ሲሆን ሙሉ ትርጉሙ ''የማር አምባ'' ማለት ነው:: ከዚያን ጊዘ ጀምሮ እስከአለንበት ዘመን ድረስ የግሸን ማርያም አካባቢ ወረዳ ''አምባሰል'' ተብሎ ይጠራል::
አባ ፈቃደ ክርስቶሥ በ517ዓ.ም በተራራው ላይ ወጥተው መጠነኛ ጎጆ በመቀለስ ሁለቱን ጽላቶች አስቀመጡ:: ሁለቱ ጽላቶችም ''ታቦተ ቅድስት ድንግል ማርያም እና ታቦተ እግዚአብሔር አብ'' ናቸው::
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

No comments:

Post a Comment