Saturday 21 September 2013

ወበዛቲ ዕለት

 ወበዛቲ ዕለት ....
የእመቤታችን ተአምር መስከረም ፲ 
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምበዚች ቀን ጼዴንያ በምትባል አገር ስጋ የለበሰች የምትመስል ስዕል ከሰሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ተአምር ተገለጠ።

ይህቺንም ስዕል የሳላት ወንጌላዊ ሉቃስ ነው። ወደ ጼዴንያ አገርም የመ...ጣችበት ምክንያት አንዲት ስምዋ ማርታ የሚባል መበለት ሴት ነበርችና ቤትዋንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች ናት። አምላክን የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያምንም እጅግ ትወዳት ነበር። በሚቻላትም ሁሉ ታገለግላታለች።
በአንዲት ቀንም ስሙ ቴዎድሮስ የሚባል መነኩሴ ከእርስዋ ዘንድ በእንግድነት አደረ። በመልካም አቀባበልም ተቀበለችው። በማግስቱም ስትሸኘው አባት ሆይ የምትሄደው ወዴት ነው? አለችው። እርሱም በከበሩ ቦታዎች ውስጥ ልሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም እሔዳለሁ አላት። እርስዋም ከእኔ ገንዘብ ወስደህ የእመቤታችን ማርያምን ስዕል ግዛልኝና በመመለሻህ ጊዜ አምጣልኝ አለችው። እርሱም በራሴ ገንዘብ ገዝቼ አመጣልሻለሁ አላት። ከዚህም በኋላ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከቅዱሳት መካናት ተባረከና ሥዕሏን ሳይገዛ ወደ ጐዳናው ተመለሰ። ያን ጊዜም ሥዕል መግዛት ህን ለምን ረሳህ የሚል የሚያስደነግጥ ድምጽ ሰማ።

ወደ ገበያም ተመልሶ ላሕይዋና መልኳ ያማረና የተወደደ የሆነ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል አግኝቶ ገዛት። በሐርና በንጹሕ ልብስም ጠቀለላት።
በጐዳናውም እየተጓዘ ሳለ ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ወንበዴዎች ተነሱበት ሊሸስም ወደደ ከዚያችም ሥዕል መንገድህን ሒድ የሚል ቃል ወጣ የተከተለውም ሳይኖር መንገዱን ተጓዘ። ሁለተኛም ነጥቆ ሊበላው አንበሳ ተነሣ ያን ጊዜም ከዚያች ሥዕል የሚያስፈራ ድምጽ ወጥቶ አንበሳውን አባረረው።
አባ ቴዎድሮስም ይሄነን ሁሉ ድንቅ ተአምር በአየ ጊዜ ያቺን ሥዕል ወደ አገሩ ሊወስዳት ወደደ ።ግዛልኝ ላለችው መበለት ይሰጣት ዘንድ አልፈለገም።
ከዚህም በኋላ በመርከብ ተሳፍሮ በሌላ አቅጣጫ ሲጓዝ ታላቅ ንፋስ ተነሣበት ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያም ወሰደው። ከመርከብም ወርዶ ከብዙ ፡ አንግዶች ፡ ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ሄደ። ማንነቱንም አልገለጸላትም። እርሷም አላወቀችውም።

በማግስቱም ተሠውሮ ወጥቶ ወደ አገሩ ሊሔድ በፈለገ ጊዜም የቅጽሩን ደጃፍ አጥቶ ሲያጥመሰምስ ዋለ። በመሸም ጊዜ ወደ ማደርያው ተመለሰ። አንዲህ ሆኖ እስከ ሦስት ቀን ኖረ። በመሸ ጊዜ በሩን ያየዋል። ነግቶ መሔድን ሲሻ የበሩ መንገድ ይሠወረዋል። ያቺም መበለት አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን? ስትቅበዘበዝ አይሃለሁና ምን ሁነህ ነው? አለችው። ከዚህም በኋላ ከዚያች ሥዕል የሆነውን ሁሉ ነገራት። ራሱንም ገለጠላት። ያቺንም ሥዕል ሰጣት። ተቀብላም የተጠቀለለችበትን ልብስ ስትፈታ ፈሳሽ ወዝ ከስዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች። ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የዚያን መነኩሴ እጆቹንና እግሮቹን ሳመች። ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር የምትቀመጥበትን አዘጋጅታ አኖረቻት ማንም እንዳይዳስሳትም የነሐስን መስኮትን ሰራችላት። በሌሊት የሚያበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች። ከመቅረዞችም ውጭ የሐር ፡ መጋረጃን ጋረደች ከሥዕሊቱ እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሰራ ወጭት አኖረች። ያም መነኮስ እስከሚሞትበት ቀን ፡ ድረስ ፡ የእመቤታችንን ድንግል ማርያምን ሥዕል እያገለገለ ኖረ።
የሀገሩም ሊቀ ጳጳሳት የዚያችን ሥዕል ዜና በሰማ ጊዜ ከኤጲስቆጶሳትና ከካህናት ከሕዝቡም ሁሉ ጋር መጣ በሠሌዳም ውስጥ ሆና አገኙዋት ከዚህ ከአምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ። ከዚያም ቅባት ቀድተው ለበረከት በተካፈሉ ጊዜ ወዲያውኑ በውጭቱ ውስጥ ይሞላል። ወደ ሌላ ቦታ ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜ ንውጽውጽታ ሁኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ በዚያች አገር ትኖራለች።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን!!!
እኛንም በእናቱ በድንግል ማርያም ጸሎት ይማረን!!!

No comments:

Post a Comment